አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመጪው በልግ ወቅት በአብዛኛው የአገሪቱ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛው በታች እርጥበታማ የአየር ጠባይ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም ÷ በመጪው በልግ ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛው በታች ዝናብ ይጠበቃል፡፡
ለዚህም በዋናነት እንደ ምክንያትነት የሚወሰደው መጪው የበልግ ወቅት በትሮፒካል ፓሲፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛው በታች መቀዝቀዝ እና ሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛው የአየር ጠባይ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ተፅዕኖ ስር ሊቆይ እንደሚችል በመጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህም ሁኔታ በተለይም በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት የሰሜን-ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ በደረቃማ የአየር ጠባይ ተጽዕኖ ስር ሊቆዩ እንደሚችሉ ይጠበቃል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
በተጨማሪም በልግ ዋናኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት ለደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንዲሁም የመካከለኛውና የደቡብ ደጋማ አካባቢዎችን ወደ መደበኛ ያደላ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበያው ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ የሰሜን ምዕራብ ፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የምስራቅ፣ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከመደበኛው በላይ ሊመዘገብ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
እንደ ኢቢሲ ዘገባ በተጨማሪ በልግ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛው በታች ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል የኤጀንሲው ትንበያ ያመላክታል፡፡
በበልግ ወቅት ከመደበኛው በታች ዝናብ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ በመሰብሰብ እንዲጠቀሙበት ምክር የተሰጠ ሲሆን፣ በወቅቱ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለማይኖር የጎርፍና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች እንደማይኖሩ ይጠበቃል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!