አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በቀጣይ ዓመታት የሚመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ እንዲያደርግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ፡፡
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የቀጣይ 10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ዙሪያ ከወረዳና ከዞን ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ አስር ዓመታት የህብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በክልሉ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2012 ዓመተምህረት ድረስ በሁለት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመናት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቢቆዩም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ውስንነቶች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የስራ እድል በመፍጠርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ ቢሆንም ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት የእቅድ ትግበራ ዓመታት የተገኙ ጥንካሬዎችና መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይ አስር ዓመታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!