የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናዋ ትምህርት ቢሮ ከርዕሳነ መምህራን ጋር በመማር ማስተማር ዙሪያ ውይይት አካሄደ

By Abrham Fekede

February 10, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በትምህርት ቤቶች በሚታዩ የመማር ማስተማር ችግሮች እና ሊተገበሩ በሚገባቸው መፍትሄዎች ዙሪያ ከርዕሳነ መምህራን ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

ርዕሳነ ምምህራኖቹ ከሁሉም የመንግስት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተውጣጡ ናቸው፡፡

ከርዕሳነ መምህራኖቹ በተጨማሪ ከክፍለ ከተማ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪዎችም በውይይቱ ተካፍለዋል፡፡

የከተማዋ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ ውይይቱ ችግሮችን በተገቢው መንገድ ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

በየትምህርት ተቋማቱ ያሉ አመራሮች ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት አቶ አዲሱ በመንግስትም ሆነ በህዝብ የሚመደብላቸውን ከፍተኛ ሀብት በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ የማይሆኑ ላይ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ነው ያስታወቁት፡፡

የትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኜ ገብሩ በበኩላቸው በመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ ለመሆን ያለውን የሰው ሀይል ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ በመማር ማስተማር ሂደቱ በመታየት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ችግሮች የተጠቀሱ ሲሆን በዋናነትም የ9ኛ ክፍል ትምህርት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች አለማስጀመር፤ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች መምህራን የትምህርት እቅድ ያለማዘጋጀት እና በአግባቡ ክፍል ገብቶ አለማስተማር ተነስተዋል፡፡

እንዲሁም በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ ለመማር ማስተማር ስራው የሚያገለግሉ ግብዓቶችን በአግባቡ ያለመጠቀም የሚሉና ተዛማጅ ችግሮች መነሳታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!