አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በትግራይ ክልል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት መስጠት እየተመለሱ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
የጤና ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የጤና ሚንስቴር እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመሆን የቀን ተቀን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ዶክተር ሊያ በማህበራዊ ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ መድሃኒቶች እና የህክምና መገልገያዎች የሚያሰራጩ የመቀሌ እና የሽሬ የመድሀኒት አቅርቦት ቅርንጫፎች የግብዐት ስርጭት እንዲፋጠን በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ተቋማት ወደ አገልግሎት ሲገቡ የደም አቅርቦት ላይ ችግር እንዳይፈጠር በክልሉ የሚገኙትን የደም ባንኮች ወደ ስራ ማስገባት እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በሚገኙ ደም ባንኮች ለማይሸፈኑ ፍላጎቶች ከማዕከል ደም እየተላከ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
እስካሁን በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል የመድሃኒትና ግብዓት ስርጭት ተደርጎ ወደ ስራ የገቡ ጤና ተቋማት 88 ደርሰዋል፡፡
በአምስቱም ዞኖች በአጠቃላይ ካሉት 40 ሆስፒታሎች ውስጥ 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ እና 5 ሆስፒታሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች 68 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩም ነው የጠቀሱት፡፡
ዶክተር ሊያ በመጨረሻም ሌሎች ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች በአጭር ጊዜ ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የጤና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር፤ ኤጀንሲዎቹ እና የጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!