አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የአንድነትና የትብብር ማሳያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ አንደሚገባ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ገለጹ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በሚኖረው የአምስት ወራት ቆይታ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
“በክልሉ ባለፉት 10 ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማስተካከል ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ርብርብ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
ዋንጫው በየወረዳው ለ10 ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በዚህም የሚከናወኑ ስራዎች በየቀኑ እንደሚገመገሙ አመላክተዋል።
“በተለይም የወረዳ አመራሩ የሀይማኖት አባቶችን የሀገር ሽማግሌዎችን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ከጎኑ በማሰለፍ እና ህዝብን በማሳተፍ የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ የሆነውን ግድብ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መንቀሳቀስ ይገባል” ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር “ግድቡ በተለይም ህዝቡ ለዘመናት አባይ ውሃ ላይ የነበረውን ቁጭት የሚሽር ነው” ብለዋል።
ከግድቡ ጅማሮ አንስቶም ያለ ልዩነት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ ጠቁመው ባለፉት ስድስት ወራትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 78 ነጥብ 3 በመቶ ላይ ደርሷል” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ “በመሆኑም ህዝቡ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ይገባል” ብለዋል፡፡
የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱማሊክ መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት 10 አመታት በመደበኛና በተዘጋጁ የተለያዩ ኩነቶች ከ55 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ከበጀት፣ ከአደረጃጀትና ከሎጅስቲክ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቁመዋል፡፡
በዋንጫው 5 ወራት የክልሉ ቆይታ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቆሙት ኃላፊው ከዚህ ውስጥም 12 ሚሊዮን ብር እንደ ክልል በሚከናወኑ የገቢ ማሰባሰብ ተግባራትና 8 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ በወረዳዎች ደረጃ የሚሰበሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ የተገኘውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ አመራሮችም እቅዱን ለማሳካት በቁርጠንነት እንደሚነቀሳቀሱ ያረጋገጡ ሲሆን በእለቱም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለክልሉ ሀኪም ወረዳ አስረክበዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መተግበሪያን https://play.google.com/store/apps/details… በስልክዎ በመጫን ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ኤፍኤም 98.1 እና ብሄራዊ ሬዲዮን ይከታተሉ፡፡ ቪዲዮዎችንም ይመልከቱ፡፡ ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!