የሀገር ውስጥ ዜና

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ አልሆነም – የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

By Abrham Fekede

February 16, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ መሆን እንዳልጀመረ አስታወቀ።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ይህንን ያለው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በማስመልከት በተካሄደ ውይይት ላይ ነው ተብሏል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት 2012 ዓ.ም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።

ይሁንና አዋጁ እስካሁን ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም፣ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም፣ ወደ ፍርድ ቤትም ጉዳዮች እየመጡ አይደለም፤ የሚሉ ጥያቄዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይሁን ይርጋ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እስካሁን ተፈጻሚ ያልሆነው በቅድሚያ ስለ አዋጁ ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ ነው ብለዋል።

በአዋጁ ዙሪያ የግንዛቤና የስርጸት ስራ ሊጀመር በታሰበበት ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ግንዘቤ የመፍጠር ስራው ሊሳካ አለመቻሉን አስረድተዋል።

በክልሎች በአዋጁ የሕግ ጥሰት የተፈጸመባቸውን ጉዳዮች የመመርመርና አንዳንዶቹን ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ ሁኔታ ቢኖርም ቅድሚያ ማስተማር አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዮቹ እንዲያዙ መደረጋቸውንና የግንዛቤ ስራዎችን በስፋት በማከናወን አዋጁ በፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን እንደሚደረግ ነው አቶ በላይሁን ያስረዱት።

የጥላቻ ንግግር ትርጓሜ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ተግባራትን ከግምት ያስገባና አስፈላጊው ትርጓሜ ላይ ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል።

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ‘የጸረ-ሽብር አዋጅን የተካ ነው’ የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳልሆነና አዋጁ በመናገር ነጻነት ላይ ገደብ እንዳልጣለም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ሁለቱ አዋጆች መንግስት በተለያዩ መስኮች ባደረጋቸው ማሻሻያዎች ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያሉ ብለዋል።

ለአዋጆቹ ከዝግጅት እስከ ማፅደቅ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው ወደ ስራ እንዲገቡ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/

ዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም https://t.me/fanatelevision

ትዊተር https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!