የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ከተማ የአድዋ ፓርክ ተሰየመ

By Abrham Fekede

February 17, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክትር ሂሩት ካሳው እና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተገኙበት በጋምቤላ ከተማ የአድዋ ፓርክ ተሰይሟል፡፡

ፓርኩ የተሰየመው 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል በጋምቤላ ክልል በድምቀት በተከበረበት ወቅት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የበዓሉ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በዓሉን ጀግኖች አባቶች የነበራቸውን አንድነት፣ አብሮነት፣ አይበገሬነትን በሚያወድስና በሚዘከር መልኩ ይከበራል ማለታቸው ይታወሳል።

በዓሉ ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ስፖርታዊ ትርዒቶች እና ባህላዊ ትዕይንቶች ተከብሯል፡፡

አድዋ “አድዋ የህብረ-ብሔራዊ አርማ” በሚል መሪ ቃል ነው 125ኛው የድል በዓል እየታሰበ የሚገኘው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት የጋምቤላ ክልል ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ያረጋገጥንበት እና ለአድዋ ከፍተኛ ቦታ መስጠቱን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው አድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የድል በዓል በመሆን ለመጠበቅና ሁልጊዜም ለማሰብ  ይረዳ ዘንድ ክልሉ ፓርክ መሰየሙን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ሚኒስትሯ በክልሉ የሚገኘውን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወይንም በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ በቤልጂየም ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የኮንጎ ወታደሮች፣ ጦርነቱ ሰለባ የሆኑ የግሪክ፣ የሶሪያ፣ የዓረብ ነጋዴዎች እና የእንግሊዝ ወታደሮች መካነ መቃብርን ጎብኝተዋል፡፡

በፀጋዬ ንጉስ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!