አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህር ዳር ከተማን የተፈጥሮ ውብ ገጽታ እና የመስህብ ስፍራዎችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ከዲ ኤስ ቲቪ የልዑካን ቡድን ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ባህር ዳር ከተማ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ታስተናግዳለች፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ቡድኖችም ወደ ከተማዋ ገብተው ልምምዳቸው እያደረጉ ይገኛል፡፡
ይህም የከተማዋን የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃቱ የተገለፀ ሲሆን ይህን መልካም አጋጣሚ የከተማዋ ማህበረሰብ በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ውድድሩን ዲ ኤስ ቲቪ በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡
ይህንኑ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እና የከተማዋን ውብ ገፅታና የተፈጥሮ መስህቦችን በየጨዋታዎቹ መጀመሪያ እና የእረፍት ሰዓት ላይ ለማስተዋወቅ መግባባት ላይ መደረሱን የከተማዋ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ዲ ኤስ ቲቪ ከ30 ሰከንድ እስከ 1 ደቂቃ ድረስ ከተማዋን በየጨዋታዎቹ መጀመሪያ እና የእረፍት ሰአት ላይ የሚያስተዋውቅ ይሆናል፡፡