የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት በመረጃ ልውውጥና በአቅም ግንባታ መስኮች የገቡትን ስምምነት ተግባራዊ ወደ ማድረግ ተሸጋገሩ

By Abrham Fekede

February 18, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት ቀደም ሲል በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በሰው ኃይል የአቅም ግንባታ ዘርፍ ተባብረው ለመሥራት የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊ ወደ ማድረግ መሸጋገራቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።

የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በደቡብ ሱዳን የውስጥ መረጃ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል አኮል ኮር ኩክ የተመራውን የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ የፀጥታ አካላት ልዑካን ቡድንን በዛሬው ዕለት ተቀብለው በሁለትዮሽና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

የሁለቱ አገራት የመረጃና ደህንነት ኃላፊዎች ከሶስት ሳምንታት በፊት በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ  ለመለዋወጥ፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንዲሁም አካባቢያዊ ስጋቶችን ለማስወገድ የደረሱትን  ስምምነትም ወደ ተግባር  በመቀየር  የሄዱበት  እርቀት ላይም  ምክክር አድርገዋል።

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና የደህንነት ተቋማት ህገወጥ የሰዎችና  የጦር መሣሪያ ዝውውሮችን ጨምሮ ሽብርተኝነትንና በድንበር አካባቢ የሚታዩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ቀጣናዊ ሰላምንና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩልም ውጤታማ ሥራዎችን መሥራታቸውን ኃላፊዎች በጋራ ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ስትራቴጂክ  አጋርነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመረጃና ደህንነት ዘርፎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው እየሰሩ  ስለመሆኑ  በውይይቱ ወቅት ተመልክቷል ።

ከውይይቱም በኋላ የደቡብ ሱዳን የውስጥ መረጃ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል አኮል ኮር ኩክ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘውን የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የጎበኙ ሲሆን፤ በጉብኝቱ ወቅትም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንቱ በአቶ ወንደወሰን ካሳ ዩንቨርሰቲ ኮሌጁ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለፃ ተደርጓላቸዋል፡፡

በኢንስቲትዩት ደረጃ በነበረበት በ1977 ዓ.ም ወቅት በመረጃ ዘርፍ ሥልጠና መውሰዳቸውን በጉብኝቱ ወቅት የገለፁት ጀነራል አኮል ኮር ኩክ፤ አሁን በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ደረጃ በማደጉ ልዩ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅም በመረጃና ደህንነት የጥናትና ሥልጠና ዘርፎች  በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ  ለደቡብ ሱዳን  የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጀነራል አኮል ኮር ኩክ የተናገሩ ሲሆን፤ አገራቸው የመረጃ ኦፊሰሮችን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የማሰልጠን ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የረጅም ግዜ ታሪካዊ  ወዳጅነት የመሠረቱ ከመሆናቸውም  በላይ ደቡብ ሱዳን  ነጻ  እንድትወጣ  በማድረግ እንዲሁም ነፃነት ካገኘች በኋላም በአጋጠማት የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅትም ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ከፍተኛ  አስተዋጽኦ  ያበረከተች በመሆኗ፤ አገራቸው ውለታዋን እንደማትረሳ ጀነራል አኮል ኮር ኩክ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት  በላከው መረጃ አመልክቷል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!