አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል መንግሥት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች 20 ሚሊየን ብር እና 2 አምቡላንሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 225ኛ መደበኛ ስብሰባዉ ነው በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ ያስተላለፈው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ መስተዳድር ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
የደቡብ ክልል ህዝብ እና መንግሥት ባሳለፍነው ጥር ወር በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ግምታዊ ዋጋው የ11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ የምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ማሳየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በትግራይ እና በደቡብ ክልል ህዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር ይበልጥ ለማጎልበት እና ያጋጠመውን ጊዜያዊ ችግር ተጋግዞ ለመፍታት በማለም ነው ድጋፍ እያደረገ ያለው፡፡
የክልሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ድጋፍ የሚሹ ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡