አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “የትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል” ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጥሪ አቀረቡ።
ዶክተር ሙሉ ነጋ በትግራይ ክልል የተደረገውን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ተከትሎ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የደረሰውን ችግር ለመፍታት የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
በዚህም የፌዴራልና የክልል መንግስታት በክልሉ መልሶ ግንባታና ሰብዓዊ ድጋፍ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራ የሚያደናቅፍና ህዝቡን ወደባሰ ችግር የሚከት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ “ወደ ህሊናቸው ሊመለሱ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የህግ ማስከበር ስራው የትግራይን ህዝብ ነጻ የሚያወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ “የሕወሓትን ጁንታና የትግራይን ህዝብ ለይቶ ማየት ይገባል”ም ነው ያሉት።
የትግራይ ህዝብ ለችግር የተዳረገው ውስን የህወሓት ሰዎች በፈጠሩት ችግር እንደሆነም ነው ያነሱት ።
በመሆኑም የትግራይ ዳያስፖራዎች “የትግራይን ህዝብ የሚወዱ ከሆነ ከፖለቲካ ጩኸት ወጥተው ድጋፍ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል ዶክተር ሙሉ።
የትግራይ ህዝብ በዚህ ሰዓት የሚረዳው እንጂ የትግራይ ዳያስፖራዎች የሚከተሉት አካሄድ እንደማይጠቅመው ገልጸዋል።
በመሆኑም ቀሪ የጥፋት ሃይሉን መደገፍና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልሉን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ማደናቀፍ ህዝቡን ለከፋ ችግር መዳረግ እንደሆነ አውስተዋል።
“ሰብዓዊነት የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም” ያሉት ዶክተር ሙሉ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ለትግራይ መልሶ ማቋቋም እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!