የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትና በማይካድራ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ተሳትፎ አላቸው በተባሉ አካላት ላይ በቀጣዮቹ ሳምንታት ክስ ይመሰረታል

By Tibebu Kebede

February 25, 2021

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በማይካድራ ከተማ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ተሳትፎ አላቸው በተባሉ አካላት ላይ በቀጣዮቹ ሳምንታት ክስ እንደሚመሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እየተደረገ ያለውን የማጣራት ሂደትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃ ማጣሪያ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ መውሰዱን አስታውሷል፡፡

የዚሁ አካል የሆነና በክልሉ ተፈጽመዋል ከተባሉ ወንጀሎችና ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የማጣራትና የምርመራ ሂደትም፥ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በፌደራል ፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መደረጉን እና ተቋማቱም የደረሱባቸውን የምርመራ ግኝቶች ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸውንም ነው ያስታወሰው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በድርጊቱ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግና ህግን ከማስከበር አንጻር የማጣራትና የምርመራ ሂደቱ መቀጠሉንም አስረድቷል፡፡

በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በማይካድራ ከተማ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አካላትም በቀጣዮቹ ሳምንታት ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጸው፡፡

ህግን ከማስከበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎንም የሚመለከታቸው ተቋማት ወንጀሎቹ በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ትክክለኛውን እና እውነተኛውን መረጃ ለማሰባሰብ አስፈላጊውን ማጣራት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉም ነው ያለው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በአክሱም ከተማ ተፈጽሟል ከተባለው ጾታዊ ጥቃትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የቀረቡ ውንጀላዎችን ከዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ጋር በመሆን እያጣራ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ፌደራል ፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግም በተመሳሳይ ምርመራዎችን እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስም በምርመራ እና በማጣራት ሂደት ያገኙትን ውጤት ለህዝብ ማሳወቃቸውን እንደሚቀጥሉም አንስቷል፡፡

መንግስትም ተቋማቱ ከሚያቀርቡት የምርመራ ውጤትና ግኝት በመነሳት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ይወስዳልም ብሏል፡፡

በማይካድራ ከተፈጸመው ወንጀል ጋር በተያያዘ 36 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!