የሀገር ውስጥ ዜና

የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የመጀመሪያ ክልላዊ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው

By Meseret Awoke

February 26, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላትን ሁለንተናዊ ተሳተፎ የማሳደግ ዓላማ ያለው የመጀመሪያው ክልላዊ የዳያስፖራ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከ3 ሚሊየን በላይ የዳያስፖራ አባላት ያሏት ሲሆን፤ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሰፊ ቁጥር ያላት ሃገር ናት፡፡

ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት በትውልድ ሃገራቸው ላይ ያላቸው ተሳትፎ በየጊዜው አያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።

“የዳያስፖራ አባላት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ መጠን መጨመሩንና የንግድና ኢንቨስትመንት አቅማቸውን ሃገራቸው ላይ ማዋል መጀመረቻወን ጠቅሰው፤ የክህሎት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ሚናቸው የጎላ ሆኗል” ብለዋል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ የክልሉን 30 በመቶ አጠቃላይ ምርት እንደሚሸፍንና ለሃገሪቷ እድገትም የማይናቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና በሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ሥራ የጀመረው የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ ፕሮግራም የአባላቱን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ብቻ በዓለም ላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት የሄዱ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሃገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በሦስት እጥፍ ማደጉንም ጠቁመዋል።

ይህም በፈረንጆቹ 2019 የዳያስፖራ አባላት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ወደ 550 ቢሊየን ዶላር ከፍ ብሏልም ነው ያሉት።

“ይህም የተቀባይ ሃገራትን የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም የልማት አጋዥነት ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው” ብለዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሃገራቸው ማስገባት እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በ3 ሺህ 186 አዳዲስ የሂሳብ ቁጥሮች ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር በላይ ሲቆጥቡ፥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ89 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!