የሀገር ውስጥ ዜና

የአድዋ ድል በዓል ብዙ በየጊዜው ተመንዝረው የማያልቁ ጥልቅ ረቂቅ ሚስጥሮች ያሉት ድል ነው-ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

By Meseret Demissu

March 02, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የአድዋ ድል በዓል ሁላችንም እንደምናውቀው ብዙ በየጊዜው ተመንዝረው የማያልቁ ጥልቅ ረቂቅ ሚስጥሮች ያሉት ድል ነው ሲሉ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሰላም ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት “በስልጡን ምክክር አዲስ ተስፋ ምዕራፍ “በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ተከታታይ ቀናት  ሲካሄድ የነበረውን ምክክር አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።

ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል  መድረኩ ከየካቲት 20 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት መካሄዱን አስታውሰው ÷  ከሁሉም የሀገሪቱ  አካባቢዎች ሁሉን የህበረተሰብ ክፍሎች የወከሉ፣ ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከቶች የወከሉ ተሳታፊዎች የታዳሙበት መድረክ እንደነበር ገልፀዋል።

መድረኩ  የአደዋ የድል በዓልን ታሳቢ በማድረግ የመድረኩን መሰረታዊ እሳቤ ከአድዋ የድል በዓል ጋር ለማስተሳሰር ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል ፡፡

የአድዋ የድል በዓል ሁላችንም እንደምናውቀው ብዙ በየጊዜው ተመንዝረው የማያልቁ ጥልቅ ረቂቅ ሚስጥሮች ያሉት ድል ነው ብለዋል

የአድዋ ድል ከበዓልነት ባሻገርም ለኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካዊያን ለመላ ጥቁር ህዝቦች መለያ የሆነ ደማቅ ታሪክ ነው ሲሉ ገልጸዋል

ኢትዮጵያ ለዓለም ነፃነት ፍትህ ፈላጊ ህዝቦች በሙሉ ካበረከተቻቸው  ስጦታዎች አንዱ አድዋ ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ የዚህ የጥንካሬ እና የድል ተምሳሌትነት መንስኤ ፣ልምዶችና እሳቤዎች አሁን ላለው ትውልድ ምን ትርጉም አላቸው የሚሉ ጉዳዮችን ለማየት ያመች ዘንድ “በስልጡን ምክክር አዲስ ተስፋ ምዕራፍ “በሚል መሪ ሀሳብ ብሔራዊ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ይህ መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከማህበረሰብ ተወካዮች ፣ልሂቃንና የመንግስት አገልግሎት ተኮር ተወካዮች ጋር ለ3 ቀናት ይካሄድ እንጂ ፣ላለፉት ስድስት ወራት ሰላም ሚኒስቴር በተለያየ ደረጃ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ሆኖ የማስተባበር ሚናውን እየተወጣ ምክክሮች ሲካሄዱ   መቆየቱ ተመላክቷል።

እነዚህ የምክክር መድረኮች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር  ትልቅ አስተዋፆ  እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን ÷ መሰል የምክክር መድረክ  ከዚህ በኋላ ቀጣይነት እንዳለውም ተገልጿል፡፡

በዚህ በሶስት ቀን ቆይታ በነበረው ምክክር ተሳታፊዎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው አጀንዳ አመጭነት የተካሄደ ውይይት መሆኑን  ደጋግመው ያረጋገጡበት ፣ የማህበረሰብ ክፍሎች ሁሉም አካባቢ ላይ ያለው ችግር ተመሳሳይነት አለው የሚለውን እውነታ ያረጋገጡበት፣ላጋጠሙ ችግሮች ለመፍሄው በጋራ መቆም አለብን በማለት የአንድነትና የጋራ አመለካከት የተገነባበት መድረክ እንደነበረ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!