አዲስ አበባ ፣ የካቲት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመቀነስ ማኅበረሰብ አቀፍ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል ብሔራዊ የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት “በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል እጅግ የከፋና ዜጎችን በተስፋ ወደማያውቁት ሀገር ህልም በመውሰድ ለሰቆቃ እየዳረገ” መሆኑን አውስተዋል ብለዋል።
ድንበር ተሻግሮ መሥራትን በሕጋዊ መንገድ ማሳካት ይቻላል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ህገ ወጥ መንገድን ከምንጩ ማድረቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሠራተኛ ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ህገ ወጥ አዘዋወሪዎች ከሞራልና ሕግ በወጣ ህሊናቸው ዜጎች ወጥተው እንዲቀሩ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
ሰብዓአዊ ፍጡር የማይሸከመው ዘግናኝ ድርጊት በህገወጥ ዝውውሩ በህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ላይ እየደረሰ እንደሆነም ገልጸዋል።
“የዜጎቻችንን ክብር ዝቅ ያደረገና ሚሊየን እናቶችን መካን ያደረገውን ችግር በቅንጅት ሠርቶ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን መንገድ መዝጋት ያስፈልጋል” ብለዋል ሚኒስትሯ።
መንግሥት ሀገር ውስጥ መሥራት የሚቻልባቸውን እድሎች በመፍጠር ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የዓለም የሥራ ድርጅች በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አሌክሲዮሙሲንዶ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ውስብስብና ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በዚህ ሂደት ከፍተኛ ተጠቂዎች መሆናቸውን በመጥቀስም፥ ቀድሞ የመከላከል ሥራ መሥራት ቁልፉ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና እያንዳንዱ ዜጋ ኀላፊነቱን መወጣት አለበትም ነው ያሉት።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!