የሀገር ውስጥ ዜና

የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከርዕሳነ መምህራን ጋር ውይይት ተካሄደ

By Abrham Fekede

March 04, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል በሚችልበት እና ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከሁሉም ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ ርዕሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

በውይይቱ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኜ ገብሩ እንዳስታወቁት ርዕሰ መምህራን በየትምህርት ቤቱ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን በበላይነት መከታተል እና ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘም ከከተማ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን የሚከታተል የአብይ እና ቴክኒክ ኮሚቴ እንደሚዋቀርም በመግለጽ በቅርቡ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ያለ ምንም እንከን እንዲካሄድ ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል፡፡

ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ በበኩላቸው የመማር ማስተማር ሂደቱን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮችን ቀድሞ መለየት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በየትምህርት ቤቱ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት መስራት እንደሚገባም ነው ያረዱት፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ የውይይት መድረክ የትምህርት ሴክተሩ የቢኤስሲ እቅድ በአቶ ፀጋዬ አሰፋ የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐር ቪዥን ቡድን መሪ ቀርቦ ተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ውይይት አድርገው መርሀ ግብሩ ፍጻሜውን ማግኘቱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!