አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሁሉም ዜጋ ከጸብ ይልቅ ሰላምን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከንፉግነት ይልቅ ማድረግን የሚመርጥ ትውልድ እንዲኖር የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበት ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “ለሰላም እንሰራለን፣ በሰላም እንኖራለን፤ዘረኝነትን እንጸየፋለን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከየትኛውም ሃገር በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖቶች መቻቻል እና አብሮ መኖር እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሃገር መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ለዘመናት የዘለቀውን የህዝቦችን መቻቻል፣ መከባባርና አንድነት ለማስቀጠል የሃይማኖት አስተምህሮ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡
“ሃገራችን እርቅ ሰላም ያስፈልጋታል፤ ኢትዮጵያ ከልዩነት የተላቀቀች ሃገር እንድትሆን እንፈልጋለንም” ብለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡
በኢትዮጵያ ሰላምና መቻቻል እንዲሰፍንም ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጉባኤው ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ትኩረቱን የሰላምና የመከባበር እሴት መገንባት ላይ አድርጎ ቆይቷል፡፡
እሴቶችን በማጠናከርም ከፍተኛ አወንታዊ ለውጥ የታዩባቸውን መንገዶች ማስመዝገቡም ተነስቷል፡፡
በመልካምነት፣ በስነ ምግባርና በሰላም ላይ የተሰሩ ስራዎች ላይ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የነበሩ ክፍተቶችን በማሻሻል ወደፊትም የሃገሪቱ ሰላምና የአብሮነት እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራልም ተብሏል፡፡
በአምስት የሃይማኖት ተቋማት የተመሰረተው ጉባኤው አሁን ላይ ሰባት የሃምናት ተቋማትን አካቷል፡፡
በመድረኩ ላይ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትም እውቅና የመስጠት መርሀ ግብር ተከናውኗል።
በዘቢብ ተክላይ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!