የሀገር ውስጥ ዜና

የመተከልን ሰላም ለመመለስ የተቋቋመው ግብረ ሃይል የሁለት ወራት ስራዎችን ገመገመ 

By Abrham Fekede

March 10, 2021

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመተከልን ሰላም ለመመለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የ70 ቀናት ሪፖርትን በግልገል በለስ ከተማ ገመገመ፡፡

በሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የሚመራው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በቀጠናው አንጻራዊ ሰላም እንደመጣም በሪፖርቱ ተመልክቷል።

በህግ ማስከበርና ጸጥታን ማስፈን፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግብረ ሃይሉ ባደረገው እንቅስቃሴ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መመለሱም ነው የተገለጸው፡፡

ውይይቱን ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ፣በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ እና የግብረ ሃይሉ ህዝባዊ ውይይት መሪ አቶ ተስፋየ በልጅጌን ጨምሮ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን አብዲሳ መርተውታል፡፡

በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 183 ቀበሌዎች መካከል 164ቱ ቀበሌዎች ላይ የአመራር መልሶ ማደራጀት ስራ በመስራት እና በ75 ቀበሌዎች ላይ ደግሞ  የእርቀ ሰላም ኮንፍረንስ ተካሂዷል ነው የተባለው።

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን የሚመስል ከ10 ሺህ በላይ የሚሊሻ አባላት ስልጠና የተሰጠ መሆኑን በመግለጽ፣ ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረጉ ስራ እንደቀጠለ መሆኑን ግብረ ሃይሉ ገልጿል።

የተቋቋመው ግብረ ሃይል በሁለት ወራት ውስጥ ባደረገው ህግን የማስከበር ስራ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠብቅ ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!