ዓለምአቀፋዊ ዜና

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ˝በኮቪድ 19 ተይዘው በኬንያ በሚገኝ ሆስፒታል ገብተዋል˝ ተባለ

By Tibebu Kebede

March 10, 2021

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ የቫይረሱን እውነተኛነ በመጠራጠርና በማጣጣል የሚታወቁት የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል መግባታቸው እየተዘገበ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በኬንያ በሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸውን የታንዛኒያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፅኑ መታመማቸውን መረጃው ደርሶኛል ያለው ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ግን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ዘግቧል።

ጆን ማጉፉሊ ላለፉት 11 ቀናት ከህዝብ እይታ የራቁ ሲሆን የኮሮና ቫይረስን በሀገራቸው የያዙበት መንገድ በበርካቶች ትችት እንዲቀርብባቸው ሲያደርግ ቆይቷል።

ታንዛኒያ ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ዕለታ ሁኔታን ይፋ ማድረግ ያቆመች ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለመግዛት ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

ፕሬዚዳንቱ የታንዛኒያ ህዝብ የኮሮና ቫይረስን ፀሎት በማድረግ እንዲከላከል ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

የሀገሪቱ መንግስትም በጉዳዮ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል ተብሏል።