አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 2 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በአገር ላይ የሚደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እንደሚያወግዙ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ የተለያዩ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና የጁንታው ቡድን ባናፈሰው ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና መንግስታት እውነታውን ባለገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዱት ሰልፍ ገልጸዋል፡፡
ድርጊቱ ተጎጂውን በዳይ አድርጎ የሚፈርጅ አቋም በመያዝ በሃገር ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳረፍ የከፈቱትን ያልተገባና ከእውነት ያፈነገጠ ጫና እንደሚቃወሙም ሰልፈኞች አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ትናንት የተካሄደው በመላው ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ በቶሮንቶ፣ በክችነር፣ በሎንዶን ኦንታሪዮ፣ በኤድመንተን፣ በሊትብሪጅ እና በካልጋሪ ከተሞች ነው፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ ተቋማትና አገራት ድርጊታቸውን እንደሚቃወሙና የጁንታው ቡድን በንጹሃን ላይ ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙ በመግለጽ ሰልፈኞቹ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ለወሰደው እርምጃ ያላቸውን ድጋፍም ገልፀዋል፡፡
ሰልፈኞች በወቅቱም የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት በተለይም የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት የሆኑት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግስታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲደግፉ የሚያሳስብ ደብዳቤም አቅርበዋል፡፡
ለቻይና፣ ሩስያና ህንድ ኤምባሲዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ላሳዩት ታማኝነትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ መከበር እንዳለበት፣ የሱዳን መንግስት በወረራ የኢትዮጵያ መሬት መያዙን እንደሚያወግዙ እና በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅና ሌሎችም መፈክሮችን በመያዝ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ መግለጻቸውን ካናዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!