አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን ከአንድ ወር ባነሠ ጊዜ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየሠራ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሀይል አስታወቀ።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በሁለት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በግልገል በለስ ከተማ እየገመገመ ነው።
በሁለት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማው በመተከል ዞን የተሠራው የህዝብ ግንኙነት ስራ 160 ሺህ ነዋሪዎችን ያሳተፈና ዞኑን ወደ ቀድሞ ሠላማዊ ሁኔታው ለመመለስ የሚያስችል አቅም የፈጠረ መሆኑ ተመልክቷል።
ኮማንድ ፖስቱ በተነሳባቸው የሠብአዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ የፀጥታ ስራ፣ የህዝብ ግንኙነት እና ከቀያቸው የተሠደዱ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋም ግቦች ውስጥ አብዛኛዎቹ የተሳካ አፈፃፀም የተከናወነባቸው ናቸው ተብሏል።
በፀጥታ ስራው ችግር ፈጣሪው ድል የተደረገበትና በፀጥታው ችግር ምክንያት እና በፀረሠላም ሀይሉ ተገደው በጫካ የነበሩ የጉምዝ ማህበረሠብ 81 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ የተቻለበት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህም አጥፊው ቡድን ማህበራዊ መሠረት እንዳይኖረው ከማስቻል ባለፈ ከቀያቸው የተሠደዱ ነዋሪዎችን ለመመለስ አቅም የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በዚህም ከ3 ሺህ 200 በላይ ታጣቂ ግለሠቦች በሠላም ለመኖር ከፀጥታ ሀይሉ እንዲተባበሩ አስችሏል።
አካባቢውን ሠላም ከማስጠበቅ ባለፈ 174 ቀበሌዎችን መልሶ ማደራጀትና መንግስታዊ መዋቅሮችን መዘርጋት መቻሉ የተገለፀ ሲሆን አገልግሎት መስጠት አቋርጠው የነበሩ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ተቋማት አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉ በጥንካሬ ተነስቷል።
ሆኖም በአመራር ክፍተትና በፀጥታ መዋቅሩ በሚታዩ የአሠራርና አደረጃጀት ችግሮች ሠላማቸው ወደ ኋላ እየተመለሱ ያሉ አካባቢዎች መኖር፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ቤቶች ፈጥኖ ማዘጋጀት አለመቻል፣ ተፈናቃዮቹ ወደ ግብርና ስራዎች ለመግባት የሚያስችለውን ጊዜ ተገማች ያላደረገ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦትን ለማቀላጠፍ የቅድመ ዝግጅት ስራ እንዲሠራ ተጠይቋል።
ኮማንድ ፖስቱ የዞኑን ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግና በቀጣይ የክልሉ የፀጥታ ሀይል ዞኑን የሚረከብበት ጀረጃ ለማድረስ የልዩ ሃይል፣ የመደበኛ ፖሊስ እና የሚልሻ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነም ኢቢሲ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!