አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ኑ አብረን እናፍጥር” በሚል መሪ ሃሳብ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የእስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች የተሳተፉበት የአፍጥር ፕሮግራም ትናንት ማምሻውን በጎዳና ላይ በጋራ ተካሂዷል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሸህ እንድሪስ በሽር እንደገለጹት፤ ረመዳን አብሮነት፣ እዝነት፣ መተሳሰብና መረዳዳትን በተግባር የሚገለጽበት ወር ነው፡፡
ህብረተሰቡ እርስ በእርስ እንዲተዋወቅና የከተማዋን ሰላም እንዲጠበቅ ለማመቻቸት በማሰብ የአፍጥር ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
እምነቱ ስለ ሰላምና አንድነት አብዝቶ እንደሚያስተምር ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የክርስትና እምነት ተከታዮችም መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ የወሎ የፍቅር የሰላምና የአብሮነት ባህላዊ እሴት እንዲቀጥል ወጣቱ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
”ወቅቱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም በቅንጅት የሚሰሩበት በመሆኑ በብሔርና ሐይማኖት ሳንከፋፈል ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
ከፕሮግራሙ አስተባባሪዎች መካከል የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ ዳዊት አራጌ በሰጡት አስተያየት፤ ወሎ አንድ ቤት ውስጥ የተለያዩ እምነቶች የሚገኙበትና ሁሉም ነገር በጋራ የሚከወንበት በመሆኑ በአፍጥር ፕሮግራሙ መሳተፋቸውን ተናግረዋልል፡፡
ሌሎች አካባቢዎችም ከወሎ ተምረው አንድነትና ሰላማቸውን በጋራ መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ወጣት ኡስማን ሁሴን በበኩሉ፤ ከህብረተሰቡ ባገኙት ገንዘብና ቁሳቁስ ሃብታሙንም፣ ድሃውንም፣ ትንሹንም ትልቁንም እኩል ጎዳና ላይ እንዲያፈጥር እድል መፍጠሩን ተናግሯል፡፡
የክርስትና እምነት ተከታዮችም ገንዘብና ቁሳቁስ ከማዋጣታቸውም ባለፈ ከሙስሊም ወንድም እህቶቻቸው ጋር ፕሮግራሙንም ማስተባበራቸውና መምራታቸው የወሎን ባህል በተግባር ማሳያቱን ገልጿል፡፡
አንድነታችንና ሰላማችን በጋራ እየጠበቅን ኢትዮጵያን ከውጭና ውስጥ ጠላት ለመጠበቅ ዝግጁ ነንም ብሏል፡፡
የደሴ ከተማ አስዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል እንዳሉት፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጎዳና ላይ የሚየደርገው የአፍጥር ፕሮግራም አንድነትና ሰላማችንን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በአፍጥር ፕሮግራሙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከመታደማቸውም ባለፈ ፕሮግራሙን ሲያስተባብሩና ሲመሩ ከመመልከት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ የውጭና ውስጥ ታሪካዊ ጠላቶቻች ኢትዮጵያን በቅንጅት ለማፍረስ እየሰሩ በመሆኑ በጋራ ተደራጅነት ለሀገራችን የምቆምበት ወቅቱ አሁን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በብሔርና ሐይማኖት በመከፋፈል ሰላምን ለመንሳት የሚሰሩ የፖለቲካ ሴረኞችን ተንኮል በማክሸፍ ከመንግስት ጎን መቆም እንደሚገባ ያመለከቱት ከንቲባው፤ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ኃለፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል መሃመድ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ያስባበሩት የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም መካሄዱ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ የሌሎች እምነት ተከታዮችም መሳተፋቸውን ጠቁመው ህብረተሰቡ አንድነትና ሰላሙን ጠብቆ የሀገሩን ዳር ድንብር ማስጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ትናንት ማምሻውን በተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም ብዛት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!