የሀገር ውስጥ ዜና

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ከሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

June 01, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ከአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው ወቅትም በቀጠናዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ በህዳሴ ግድብ፣ በህግ ማስከበር፣ በሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት፣ ከሱዳን ድንበር ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ያለበትን ደረጃ እና እየተከናወኑ ያሉት ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ የሙሌት ሥራ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቅሰው፥ የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም በማይነካ መልኩ እንደሚፈፀም ገልፀዋል፡፡

ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት አፈ ጉባዔው የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም አንስተዋል፡፡

ሴናተር ጂም ኢንሆፍ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የተሰጠው ማብራሪያ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለመረዳት እንዳስቻላቸው አውስተዋል፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!