የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረሪ ክልል 3 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

By Tibebu Kebede

June 02, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ዘንድሮ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር 3 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ገለጸ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በክልሉ ከመጪው የሰኔ ወር መግቢያ ጀምሮ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ከሚያዝያ ወር ጀምሮም የጉድጓድ ቁፋሮ እና ማህበረሰቡን የማነቃነቅ ስራ የተሰራ ሲሆን ከ500 ሺህ በላይ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ እየተዘጋጁ ካሉ 3 ሚሊየን ችግኞች መካካልም 40 በመቶው የዛፍ ቀሪው የጥምር ደን ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከተተከሉ ችግኞች መካከል 72 በመቶ መፅደቃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

በክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አባስ በሚቀጥለው ወር በሚጀመረው የአረንጓዴ አሻራ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች በአንድ ጀምበር 350 ሺህ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!