የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል መረዳት አለበት ተባለ

By Tibebu Kebede

June 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል መረዳት እንዳለበት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ጥሪ አቀረቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል ።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት መንግሥት በክልሉ ያከናወነውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ሥራ እየተሰራ ነው።

በዚህም የግብርና ሥራ ፣ ትምህርት ፣ ጤና ፣ የስልክና ኢንተርኔት እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ እየተሰሩ ቢሆንም በአንዳንድ አካላት የሚወጡ መረጃዎች በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባና ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል ሚኒስትሯ።

“ዜጎቻችን ናቸው የሚሰቃዩት፤ ስቃያቸው ይሰማናል” ያሉት ሚኒስትሯ መንግሥት የክልሉ ህዝብ ወደ ቀደመ ሰላሙና ልማቱ እንዲመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ክልሉን በተመለከተ የሚሰራጨውን መረጃ በማጣራት ትክክለኛውን መረጃ መያዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ገልጸው ለሥራዎቹ ስኬት የአጋር አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!