የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስቴሩ በመቐለ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 50 ቶን የሚገመት አልሚ ምግቦችና አልባሳት ድጋፍ አደረገ

By Meseret Awoke

June 07, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቐለ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል 50 ቶን የሚገመት የተለያየ ይዘት ያላቸው አልሚ ምግቦችና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል በማሰባሰብ ድጋፉ ማድረጉን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ እታፈንታ አሰፋ ገለፁ።

ድጋፉ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ዘይት፣ ፊኖ ዱቄት እንዲሁም የህፃናት አልሚ ምግቦችን ያካተተ ሲሆን፥ ለህፃናትና ለአዋቂዎች የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ሃላፊዋ ገልፀዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች እርዳታውን በማሰባሰብ በመተከልና አጣዬ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ጭምር እያዳረስን እንገኛለን ያሉት ሃላፊዋ፥ ለትግራይ ክልል የተሰጠው ድጋፍ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመትም ነው የገለጹት።

ድጋፉ በቀጥታ በመቐለ ከተማ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች እንደሚውል መናገራቸውን የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!