አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የመጀመሪያውን የቡና ማቀነባበሪያና የባሬስታ ማሰልጠኛ ዘመናዊ ማዕከል አስመረቀ።
በምርቃት ስነ ሥርዓቱ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴንን ጨምሮ፥ ከፍተኛ የመንግስት ባለ ሥልጣናትና የአለም አቀፍ ተቋማት ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በባለስልጣኑ ዋና መስሪያ ቤት ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን፥ የማዕከሉ መገንባት በቡና ጥራትና በዘርፉ ዘመናዊ አስተዳደር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የአገሪቱን የቡና ደረጃ በማሳደግ ከውጭ ምንዛሬ የሚገኘውን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ገልጸዋል።
የቡና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማስታወቂያ ሥራዎች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፥ በግብርናው ዘርፍ የ10 አመት የልማት እቅዱ ውስጥ ቡናን ዋና አካል በማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፥ የማዕከሉ መገንባት ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
ዘርፉን ለማዘመን፣ የአገሪቱን የቡና ጥራት ለማሳደግና የቡና አሠራር ሙያን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የቡና ማቀነባበሪያና የባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከሉ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን፥ ከስልጠና እስከ ዲግሪ ድረስ ትምህርት እንደሚሰጥ ተነግሯል።
የዩኒዶ የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አውሬላ ፓትሪዛ ካላባሮ፥ የቴክኒካል ሥራዎችን ክፍተት በመሙላት የቡና ጥራትን ለማሳደግ ይረዳል በማለት ገልጸዋል።
ማዕከሉ ዘመናዊና አለም አቀፍ ጥራትን ያሟላ በመሆኑም በሥሩ የቡና አሠራር ሙያን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል ሲሉ አሰረድተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!