አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ከ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ወይም 135 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ምግብ ሸቀጥ መሰራጨቱን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ገለጹ።
ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው የቀጥታ ስርጭት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው በትግራይ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነሩ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀበት ጊዜ አንስቶ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው፥ በሁለተኛና በሶስተኛ ዙር 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ነው የተናገሩት።
በክልሉ 170 ሺህ 798 ሜትሪክ ቶን ምግብ መቅረቡን ገልጸው፤ ለዚህም ከ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የተሰራጨው የሰብዓዊ ድጋፍ ወጪ 70 በመቶ በመንግስት እንዲሁም ቀሪው 30 በመቶ በአጋሮች እንደተሸፈነ አብራርተዋል።
በሶስተኛ ዙር ድጋፍ መንግስትን ጨምሮ ስድስት አካላት ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት። መንግስት እየተደረገ ያለውን ድጋፍ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ የእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲሳካ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
“ይህም መንግስት ከአጋሮች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሚገኝ ያሳያል” ያሉት አቶ ምትኩ፤ በአሁኑ ወቅት 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል። ከእነዚህ መካከል 1 ሚሊየን 10 ሺህ የሚሆኑት የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 436 ሺህ ደግሞ የኤርትራ ስደተኞች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች የራሳቸው በጀት ያላቸው በመሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተቱ ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!