የሀገር ውስጥ ዜና

በሚዛን አማን ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

By Tibebu Kebede

June 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰባት ሰዎችን በጫነች ባጃጅ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ በአራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን በቤንች ሸኮ ዞን ትራፊክ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ መረጃና ስታቲስቲክስ ክፍል ሀላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ይመኙሻል ክፍሌ ገልፀዋል።

አደጋው በከተማዋ በተለምዶ በርጌስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰባት ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች የሆነች ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ቆሞ ከነበረ ሲኖ ትራክ ጋር በመጋጨቷ የደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው ተሳፋሪዎች መካከል ሁለቱ ወደ ጅማ ሆስፒታል መላካቸውን ሁለቱ ተጎጂዎች ደግሞ በሚዛን ቴፒ ቲቺንግ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአደጋው መንስኤ ጠጥቶ ማሽከርከር መሆኑን የገለፁት ረዳት ኢንስፔክተር ይመኙሻል ባጃጇ መጫን ከምትችለው በላይ ሶስት ተጨማሪ ሰዎችን መጫኗ ለአደጋው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በተስፋዬ ምሬሳ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!