አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር በጋራ ባዘጋጁት ሥነ ስርዓት ላይ ለአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለገጣፎ በሚገኘው በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡
ለ91 ዓመቱ አዛውንት ስጦታው የተበረከተላቸው ለሀገራቸው በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ላበረከቱላት የረዥም ዘመን አገልግሎት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርስነት የሚያዝ የልዩ ታሪካዊ ሁነቶች ማስታወሻ የወርቅ ሳንቲም በመሸለም የወርቅ ካባም አልብሷቸዋል፡፡
አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ፣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ባለቤት ወይዘሮ ሔለን ገብረእግዚአብሔርና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አብዮቱ መምጣት ድረስ የኢትዮጵያ የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ኢትዮጵያን ወክለውን በዓለም ባንክ ውስጥ የቦርድ አባል ሆነው ሰርተዋል፡፡
ከአብዮቱ ማግስትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የናይጀሪያ ቅርንጫፍ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም በ1984 ዓ.ም. የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክን በመመስረት በግል የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ መሆን ችለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና በሕግ ዲግሪዎች የተመረቁት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በትዳር ውስጥ በቆዩባቸው ያለፉት 54 ዓመታት 6 ልጆችን አፍርተዋል፡፡
በየውብዳር ጌትዬ እና እዝራ እጅጉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!