አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ክልል ማስወጣት የተጀመረው ከአንድ ወር በፊት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ከህወሃት ጋር ግጭት ውስጥ የተገባባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት በተለየ መንገድ ከመከላከያ የሚስተካካል ተቋም ለመገንባት ወታደር ለማዘጋጀት ሰፊ ስራ መስራቱ አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም በቀጣይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፈታተን በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተለያዩ ክልሎች ቅጥረኖችን በማደራጀት በሀገሪቱ ከፍተኛ ግጭቶች እንዲነሱ እና በአካባቢ ሰላም እንዳይኖር መስራታቸው ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ሰሜን ዕዝ ላይ ጡት እስከ መቁረጥ የደረሰ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረሳቸውም እጅግ አስከፊ እንደነበነር አውስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ችግሩን ለመፍታት በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች እና በተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አማካይነት ለምነናል ግን አልተቀበሉንም” ነው ያሉት፡፡
ውጊያው እንደተከፈተ ሀገሪቱን ለማተራመስ በርካካታ እቅዶች እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚነስትሩ ይህን በቀላሉ ለማምከን ሰፊ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡
በውጊያውም ጁንታውን ነጥሎ ከመምታት ባለፈ ከተማ ውስጥ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የመንግስ ተቋማትን ስራ ለማስጀመር እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎችም ከማንም ሀገር በላይ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ለዚህም 100 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የተሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መልሶ ለመገንባትም ከ30 በላይ ሰራተኞች በጁንታው መገደላቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከህግ ማስከበር በኋላ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም ግንባር ቀደም በሆኑ ጁንታዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ወይም ለህግ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም የሰሜን እዝን እና በክልሉ የነበሩ የጦር መሳሪያዎችን ማውጣት ከመቻሉ ባለፈ መከላላከያ ሀገራዊ ቁመና ይዞ እንዲደራጅ እና እንዲጠናከር የሚያስችል መልካም ተሞክሮ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
መከላከያው ከትግራይ ክልል የማስወጣት ስራው ከአንድ ወር በፊት መጀመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የመውጣት ሂደቱ በአራት ግንባር በሶስት መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሂደት ሁለቱ ዙሮች መከላከያ መውጣቱ ሳይታወቅ በሶስተኛው ዙር መታወቁንም ጠቅሰዋል፡፡
ውሳኔው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ፣ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመቆጣጠር፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ፣ ከስደት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ለማቋም በማለም የተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እና አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዲያርሱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከሁሉ በላይም ኢትዮጵያውያንን ለመነጣጠል የታቀደውን ሴራ የተሳካ እንዳይሆን መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በአንፃሩ በክልሉ ለ40 ዓመታት የተዘራው የዘረኝነት መርዝ መንቀል አልተቻለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ለዚህም የጥሞና ጊዜ መስጠቱ ተገቢ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከደጋፊዎቹ ጋር በውጭ ሀገራት ባሰራቸው የውሸት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻው ከፍተኛ ጫና መፈጠሩንም ነው ያነሱት፡፡
አሁን ላይ የትግራይ ግጭት እንዲቆም አይፈለግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላማው የተዳከመች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!