የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለቀጠናው ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ወጣቶች

By Meseret Demissu

July 09, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር ለቀጠናው ሀገራት አረአያ እንደሚሆን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ወጣቶች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ወጣቶች መርሃ-ግብሩ ዓለምን እያስጨነቀ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ሰላም ግንባታ መርሃ-ግብር ዳይሬክተር ዶክተር ሩክስ አኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቴክኖሎጂና የህዝብ ቁጥር መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የበካይ ጋዝ ልቀት መጨመርም አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻው ጉዳይ መሆኑም ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጰያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአገሪቷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

መርሃ-ግብሩ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋ እንደሚገባ ገልጽዋል።

ዩጋንዳዊ ወጣት ጃኮብ ዬሩ ሀገሩ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ከኢትዮጵያ የተሻሉ ልምዶችን መውሰድ እንዳለባት አብራርቷል።

ዓለምን እያሰጋ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር በአረንጓዴ ልማት መከላከል ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ጠቅሰው÷ ችግሩን በአፋጣኝ መቅረፍ ካልተቻለ ትውልዱ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚጋፈጥ ይሆናል ነው ያሉት።

ችግሩ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ይበልጥ አሳሳቢ በመሆኑ ከኢትዮጰያ ልምድ መቅሰምና መተግበር  እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

የጤናና የምግብ ተደራሽነትን ለማስፋት የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የተናገረው ደግሞ የሲሼልስ ዜግነት ያለው ወጣት ያኔክ ሚሜ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል  የአረንጓዴ ልማት ስራ ወሳኝ መሆኑን ገልጾ÷ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ስራን አድንቋል።

መርሃ -ግብሩም አፍሪካዊ በሆነ አካሄድ የአፍሪካን ችግር የመፍታት ሂደት መሆኑን እንደሚገነዘብም አንስቷል።

ነገር ግን አፍሪካውያን ትልሞቻቸውን እውን ለማድረግ ግጭቶችን ማስቀረት እንዳለባቸውም ተናግሯል።

ኬኒያዊቷ ወጣት ኢቮን ቼጌ  አፍሪካውያን ወጣቶች በአነስተኛ ቦታ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ ገልጻለች።

እያንዳንዱ ሰው የሚኖርብትን አካባቢ ማልማት ከቻለ ሀገር በቀላሉ እንደምትቀየር ገልጻ÷ ከዚህ አንጻር አካባቢያችንን ለጤናና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያለችው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!