የሀገር ውስጥ ዜና

ከደህንነት ስጋት ነጻ በሆነ አካባቢ መጠለያ ሊሰጠን ይገባል…በአዲ ሃሩሽና ማይአይኒ የተጠለሉ የኤርትራ ስደተኞች

By Meseret Demissu

July 10, 2021

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጸጥታ ስጋት ነጻ በሆነ አካባቢ መጠለያ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ በአዲ ሃሩሽና ማይአይኒ መጠለያዎች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጠይቀዋል።

የስደተኞቹን ጥያቄ ለመመለስ ከደህንነት ስጋት ነፃ ወደ ሆኑ አካባቢዎች ለማዛወር ቦታ የማመቻቸትና ሌሎች የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ገልጿል።

በማይአይኒ ስደተኞች ጣቢያ ለሁለት ዓመታት የኖሩት መሪጌታ ሰለሞን ተስፋ ማርያም ለኢዜአ እንዳሉት÷ ከጸጥታ ስጋት ባለፈ የተሟላ የውሃና የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የጤናና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተሟላ መልክ እያገኙ አይደለም።

የህክምና እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች በአግባቡ እየቀረቡላቸው እንዳልሆነ ገልጸው÷ ችግራቸው እንዲፈታ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በስደተኞቹ ዙሪያ የሚሰሩና የሚመለከታቸው ድርጅቶችም ሰብዓዊ እርዳታዎችን ከማቅረብ ባለፈ መጠለያቸው ከስጋት ነፃ ወደ ሆኑ አካባቢዎች እንዲዛወር እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

ያሉበት የመጠለያ ጣቢያ አካባቢ ለስጋት የተጋለጠ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በአዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩት ቀሲስ ዳዊት ተክሌ ናቸው።

በሚመለከታቸው የረድኤት ድርጅቶች ሊደረግላቸው የሚገባው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ባለመሆኑ ለችግርና ለደህንነት ስጋት መጋለጣቸውንም ተናግረዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው÷ የስደተኞቹ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው፤ ስጋታቸውን ለማቃለል መንግስት በአማራ ክልል ዳባት ከተማ አለም ዋጭ በተባለ ስፍራ 91 ሄክታር መሬት በመረከብ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ ለመገንባት እንቅስቀሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከአካባቢው የጸጥታ ስጋት አንጻር በማይ አይኒና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ28 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞችን ደህንነት የመጠበቅ ስራ ከኮማንድ ፖስት ጋር በመነጋገር እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በአዲ ሃሩሽና ማይአይኒ መጠለያዎች ላይ እስከ አሁን ምንም ሞት እንዳላጋጠመ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤የስደተኞቹ ስጋትም ቀደም ሲል ከነበሩበት ሁኔታ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የስደተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ተግባር እንዳከናወነ ገልጸው፤ በስደተኞች ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት በገቡት ቃል መሰረት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በስደተኞች ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ቃል በገቡት መሰረት አስፈላጊውን አገልግሎት ለስደተኞች በሚፈለገው መልኩ እየሰጡ እንዳልሆነ ጠቅሰው ድርጅቶቹ የተሰማሩት ሰብዓዊ አገልግሎት ለመስጠት ቢሆንም ከዓላማቸው ውጭ ጉዳዩን ፖለቲካዊ የማድረግ ሁኔታ እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል።

አንዳንዶቹ መሬት ላይ ሳይሆን ቲዩተር፣ ፌስ ቡክና መግለጫ በመስጠት ተጠምደዋል ያሉት አቶ ተስፋሁን፤ ድርጅቶቹ ስደተኞችን በማስተናገድ በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን የማያከናውኑ ከሆነ አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በመከተል እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!