አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ በኤሮስፔስ ምህድንስና ዘርፍ የድህረ ምረቃ ትምህርት መስጠት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የሺሩን አለማየሁ በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ትምሀርት ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።
ትምህርቱ የሚሰጠው ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርስቲው ጋር በ2012 ዓ.ም በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱና ዩኒቨርሲቲው በጋራ በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ ትምህርቱን ለማስተማር የሚያስችል የስርዓት ትምህርት ቀረጻ አዘጋጅተው ለዩኒቨርሲቲው መላኩንና ዩኒቨርሲቲው ውሳኔ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የኤሮስፔስ ምህንድስና ትምህርት መጀመሩ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ክፍተት ለመሙላት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በቀጣይም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን ለመስጠት እቅድ እንዳለ ኢዜአ ዘግቧል።
በኤሮስፔስ ምህንድስና የሚሰጠው ትምህርት ኢትዮጵያ ለመገንባት ያቀደችውን የሳተላይት ማምረቻ፣ መገጣጠሚያ፣ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ነው ዶክተር የሺሩን ያስረዱት።
የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል ግንባታ ለመጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑም ታውቋል።
የኤሮስፔስ ምህንድስና የአውሮፕላን፣ የጠፈር አውሮፕላን እንዲሁም ከነዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ስርዓቶችና መሳሪያዎች ንድፍ፣ መስራት፣ ማምረትና መፈተሽ ላይ የሚያተኩር የምህንድስና ዘርፍ ነው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!