አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 5 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተከናወነው ሃገር አቀፍ ምርጫ የተቋማት ገለልተኛነት በከፊል የታየበት እንደነበር ምሁራን ገለጹ፡፡
ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች የፍትህ ተቋማት፣ የምርጫ ቦርድ እና መሰል ለዴሞክራሲ መሰረት የሆኑ ተቋማት ቀደም ባሉት ጊዜያት ስለ ገለልተኛነታቸው ጥያቄ ሲነሳባቸው ቆይቷል፡፡
እነዚህ ተቋማት በቅርብ ጊዜ መሰል ጥያቄዎችን ለመፍታትና የህዝብ አመኔታን ለማግኘት የሪፎርም ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ነጻና ገለልተኛ እንዲሁም ተአማኒ ምርጫን ለማከናወን የሚያስችለውን ታላቅ ሃገራዊ ሁነት ለማስተናገድ የተለያዩ መዋቅራዊ ለውጦችን ሲያካሂድ እንደቆየ ይገልጻል ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የህግ ባለሙያ እና አማካሪው አቶ ፋሲል ስለሺ ቦርዱ ምርጫውን ለማስፈጸም ያከናወናቸው ተግባራት ለሚፈለገው ጠንካራ የተቋማት ግንባታ ሂደት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እነዚህ መዋቅራዊ የለውጥ ስራዎች በምርጫው ምዕራፎች ላይ መታየታቸውን የጠቀሱት የህግ ባለሙያው፥ ምርጫውን አስመልክቶ ከመራጩ ህዝብም ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የዘንድሮው ምርጫ ካጋጠሙት ከጥቂት ውስንነቶች ውጭ መልካም ጎኖቹን በስፋት መነሳታቸውንም አውስተዋል፡፡
በወሎ ዮኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የህግ መምህርና ተመራማሪው አቶ ደጀኔ የማነ የዘንድሮው ምርጫ ዜጎች የሚፈልጉትን አካል ወደ ስልጣን ለማምጣት ያደረጉት ጥረት በአግባቡ ይፈጸም ዘንድ ጥረት የተደረገበት ነው ይላሉ፡፡
ይሁን እንጅ ምሁራኑ ቦርዱ ምሉዕ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
በተለይም ቦርዱ እስከ ዞን እና ወረዳ ድረስ ያሉ የአወቃቀር ስራዎች ላይ ማሻሻል የሚገባው ጉዳይ እንዳለም ገልጸዋል፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ምርጫ ያስመዘገባቸውን ውጤታማ ስራዎች ለማስቀጠል ብሎም የታዩበትን ክፍተቶች ለማስተካከል መስራት ይገባዋልም ነው ያሉት ምሁራኑ፡፡
አሁንም ድረስ በፍትህ ተቋማት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ቢኖሩም በዘንድሮው ምርጫ በተለይም ምርጫው ገለልተኛና ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ በየተቋማቱ የታዩ ተነሳሽነቶች ሊበረታቱ እንደሚገባም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡
ለሚፈለገው ጠንካራ የዴሞክራሲና ፍትህ ተቋማት ግንባታ እውን መሆንም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሃላፊነት እንዳለም ነው ምሁራኑ የሚናገሩት፡፡
በአወል አበራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!