የሀገር ውስጥ ዜና

የሲሚንቶ ግብይትን ለመቆጣጣር የወጣው መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተነሳ

By Tibebu Kebede

July 14, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ግብይትን ለመቆጣጣር የወጣው መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ መነሳቱን አስታወቀ፡፡

በዚህ መሰረት የግብይት ሂደቱ በነፃ ገበያ መርህ እንዲከናወን ተወስኗል ብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ እቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት፥ በሲሚንቶ ግብይት ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሲባል ወደ ቀደመ የነፃ ገበያ አሰራር ተመልሰናል ብለዋል ።

በዋነኛነትም የክረምት ወቅት የሲሚንቶ ፍላጎት ስለሚቀንስ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሲሚንቶ ባልተጋነነ ዋጋ እንዲሸጡ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአቅርቦቱ ላይ ያለውን ክፍተት የፋብሪካዎችን አቅም በማጠናከር ለመሙላትና ከውጪ ለማስገባት መንግስት መወሰኑን ገልጸዋል።

የፋብሪካዎች የምርት መሸጫ ዋጋም ከሚኒስቴሩ ጋር በመነጋገር በተጠና እንዲሆን ስምምነት ተደርሷልም ነው ያሉት።

አሰራሩም በነፃ ገበያ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል መወሰኑንም ተናግረዋል።

በሀይለየሱስ መኮንን እና ፈትያ አብደላ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!