የሀገር ውስጥ ዜና

ሃገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ አማራጭ የለም- አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ

By Meseret Demissu

July 16, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ የለም ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ  ገለጹ።

ሃአገር አፍራሹን ሽብርተኛ ቡድን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ በሚደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ የሶማሌ ክልልና ህዝብ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለማምከን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሶማሌ ክልል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የጸጥታ ኃይል ወደ ቦታው ለማሰመራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡

አቶ ሙስጠፌ አሸባሪው ህወሓት በሃገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው የህግ የማስከበር ዘመቻ የተለያዩ ምዕራፎችን ማለፉን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሂደት የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሰጣቸው ምክንያቶች ይለዋወጡ፣ ሀሳቦቹ ይቀያየሩ እንጂ የሚከተለው ሃገር የማፍረስ አጀንዳ በመሆኑ ሃገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ የለምም ነው ያሉት ፡፡

የሽብር ቡድኑ የሚከተለው አጀንዳ እሱ ከሚያነሳቸው ሰብዓዊ መብትና ራስን በራስ ከማስተዳደር አጀንዳዎች ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም ያሉት አቶ ሙስጠፌ ÷ እነዚህን አጀንዳዎች የሚያነሳቸው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማወናበድ እንጂ የእሱ ዓላማ ሃገርን ማፍረስ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍና ለአርሶ አደሩ እርሻ ሥራ ሲባል በመንግሥት የተደረገ ውሳኔ መሆኑን ልቡ እያወቀ ውሳኔውን እንደ ፍርሐት በመቁጠር ተደፋፍሮ ክልሎችን ለማጥቃትና ሃገሪቱን ለማፍረስ እየሞከረ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!