የሀገር ውስጥ ዜና

ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ይገባል – ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

By Tibebu Kebede

July 16, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከከተማው ከተውጣጡ ሴቶች ጋር ተወያዩ።

ውይይቱ በዚህ ወቅት ዋጋ እየከፈለ ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከጎኑ እንደሆኑ ለማሳየት እንዲሁም፤ የሃገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የጥፋት ሃይሎችን በመመከት የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ነው።

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የህወሃት የሽብር ቡድን እያደረገ ላለው የጥፋት ስራ ህጻናትና ሴቶችን መጠቀሙ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ፥ ሴቶች ይህን ድርጊት ልናወግዝ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ወቅት መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከጎኑ መሆናችንን ማሳየት አለብንም ነው ያሉት።

በተለይ በዚህ ወቅት የአካባቢን ሰላም ለማደፍረስ ከውጪም ከውስጥም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በመኖራቸው ከማንም በላይ የአካባቢን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል።

“ለመከላከያ ሰራዊቱ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እየቀጠልን የጀመርናቸውን የልማት ስራዎች እያስቀጠልን የአካባቢያችንን ሰላም በማስጠበቅ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ እውን እናድርግ” ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሴቶች፣ የህወሃት የሽብር ቡድን በትግራይ ህጻናትና ሴቶች ላይ እያደረገ ያለውን እኩይ ተግባር አውግዘዋል።

ዋጋ እየከፈለ ከሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ አሁንም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በሃይማኖት ኢያሱ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!