የሀገር ውስጥ ዜና

በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቀረበ

By Meseret Awoke

July 17, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለሚደረገው ጥረት በጥናትና በምርምር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ምክክር በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሰላም ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለ“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደው የበየነ መረብ ውይይት፥ ኢትዮጵያ ያጋጠማት ወቅታዊ ችግር ወደ ዲሞክራሲ የሚደረጉ ሽግግሮች ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ ከመገባቱ በፊት በርካታ የሰላም እድሎች ተፈጥረውለት ሊቀበል ያልቻለው የህወሀት ሽብርተኛ ቡድን በተመሳሳይ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሰው ቡድኑ ተኩስ አቁሙን በመጻረር ህጻናትን ሳይቀር ወደጦር ማሰለፍ መቀጠሉ ሊወገዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው የዘላቂ ሰላም ግንባታ የተፈጠሩ ችግሮችን ሳንፈታ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ ተገደን ወደ ህግ ማስከበር የገባንበት ሂደት ወደ ዲሞክራሲ ለምናደርገው ሽግግር እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታይ በመሆኑ ለመፍታት የመላው ህዝብ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ለውጡ ፈጣን በመሆኑ በሽግግር ላይ ያሉ ተመሳሳይ ሀገሮች ይህንን መሰል ተግዳሮት ያጋጠማቸው መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ ችግሩን በመፍታት ወደ ተሻለ የዲሞክራሲ ስርዓት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም የውጪ ጣልቃ ገብነት፣ የሂደት ጠመዝማዛ መሆን እና የሚዲያዎች አሉታዊ ሚናም በሽግግር ሂደት እክል ሊፈጥሩ የሚችሉና በአንዳንድ ሀገሮችም የተፈጠሩ ለውጦች ረጅም ሂደት የጠየቁ መሆናቸውን ማስታወሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በትግራይ ክልል ያለውን ሰላም ከማስፈን አንጻር በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተከታታይ ውይይትና መግባባት የተደረሰበት ተግባራዊ ስራዎች ተጀምረው እንደነበር አስታውሰው፥ የሽብርተኛው ቡድን እነዚህን ወገኖች የተለያየ ስያሜ በመስጠት ለማሸማቀቅ የተደረጉ ዘመቻዎችንም ጠቅሰዋል፡፡

“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በበኩላቸው፥ ለሃገራቸው ሰላምና መረጋጋት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከመዋጋት በተጨማሪ ለሚገኙበት ሀገር የፓርላማ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ዳያስፖራውን በማስተባበር ሀገሩ ለምታቀርብለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንደሰጡ እንዲሁም በቀጣይነት ሊሰሩ ያቀዷቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም ወቅታዊ መረጃን በአግባቡ ለዳያስፖራው በጊዜው አለመድረስ ዳያስፖራው የተሳሳተ መረጃን እንዲይዝ ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!