አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
አቶ ደመቀ መኮንን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ÷የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መርሃግብር በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን ብለዋል።
በቀጣይ የሃገራችንን የመልማት ፍላጎት ጥያቄን በሚመልስ መልኩ የጀመርነው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ በህዝባችን የነቃ ተሳትፎ እና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
ተፈጥሮ የሰጠችንን ታላቅ ፀጋ አልምተን ለመጠቀም በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ፣ በላባችሁና በዕውቀታችሁ ባደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችን እንኳን ደስ አለን ብለዋል።
በዚህ የስኬት ግለት ሃገራችንን ለውጪ አካላት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ መመከትና ሴራቸውን ማምከን ይገባልም ብለዋል ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ ፕሮጀክት በዚህ የስኬት ደረጃ ያደረሰ እንዲሁም በብዙ ጫናዎች ሳይበገር ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደ ህዝብ አንድነቱን አጥብቆና ጠብቆ ሲተም ለውጤት እንደሚበቃ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መመልከት ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ የሚዳፈሩ እና የውጪ አካላት ፍላጎት አስፈፃሚ የሆኑ ሃይሎች ዳግም እንዳይመለሱ ህዝቡ ተባብሮ ሃያልነቱን ማረጋገጥ አለበትም ነው ያሉት።
ባለፉት ጊዜያት ከውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሃይሎች የፈጠሩብንን ጫናዎች በጥበብ መሻገራችን አይዘነጋም፤ ወደፊትም ለሚጠብቁን ፈተናዎችም ህዝቡ ህብረቱን አጠናክሮ በንቃት መመከት ይጠበቅበታል።
ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ በመድረሳችን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፤ በዘላቂነት አንድነታችንን አጠናክረን ትውልድ እና ሃገርን በድል እንድናሻግር ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!