የሀገር ውስጥ ዜና

ውጊያ ለመክፈት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ሰብዓዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የምኒልክ ብርጌድ አስታወቀ

By Tibebu Kebede

July 22, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ትህነግ ቡድን በወልቃይት ማይጋባ በሚገኘው የተከዜ ድልድይ አካባቢ ጥቃት ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በአማራ ልዩ ኀይል ርምጃ እየተወሰደበት ነው።

የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ አሸባሪው ቡድን ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ውጊያ ለመክፈት ሞክሮ ነበር።

በአካባቢው የተሠማራው የአማራ ልዩ ኀይል ግን ሙከራውን በብቃት በመመከት በቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን የምኒልክ ብርጌድ ዘመቻ ኀላፊ ኢንስፔክተር መኮንን ምስጋናው ተናግረዋል፡፡

ኢንስፔክተር መኮንን እንዳሉት ጠላት ሕጻናትን ያለ ምግብ በሀሽሽ እያደነዘዘ ለጦርነት እየማገደ ነው።

በአካባቢው በቂ ኀይል መሠማራቱን ያስታወቁት ዘመቻ ኀላፊው የአሸባሪው ታጣቂ ቡድን ላደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሁሉ ተገቢ ምላሽ እንደተሰጠ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

አሸባሪው ቡድን በወገን ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ እንዲደርስበት ተደርጓልም ነው ያሉት።

ልዩ ኀይሉ ከክልሉ አልፎ ሀገራዊ ስሜት ወስዶ መሰማራቱን በመጥቀስም በአሸባሪው ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በሚኒልክ ብርጌድ የሁለተኛ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር ቅዱስ በለጠ እንዳሉት ጠላት የነበረውን ኀይል ተጠቅሞ አራት ጊዜ የጸረ ማጥቃት ሙከራ አድርጎ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ደርሶበታል።

ልዩ ኀይሉ አሁንም ቀጠናውን በንቃትና በብቃት እየጠበቀ እንደሆነ አብራርተዋል።

በስፍራው ስምሪት ከወሰዱ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን የማጽዳት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!