የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ሸዋ፣በማዕከላዊ ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞን የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርኃግብር ተካሄደ

By Meseret Demissu

July 22, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የሰሜን ሸዋ፣በማዕከላዊ ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞን የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርኃግብር ተካሂዷል።

“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር በሰሜን ሸዋ ዞን በአንድ ጀምበር 48 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑን  የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል።

ችግኝ የሚተከለው በ4 ሺህ 812 ሄክታር መሬት ላይ  ሲሆን በዞኑ በተያዘው ክረምት 264 ሚሊየን ችግኝ ይተከላል ተብሏል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርኃግብር ተካሂዷል፡፡

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር ከ 23 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞች በ144 የተከላ ቦታዎችና በ104 ቀበሌዎች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ነጋ ይስማው ተናግረዋል።

በሌላም በኩል  በምዕራብ ጎንደር ዞን ”ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 55 ሺህ ችግኝ በ13 የመትከያ ጣቢያዎች በ21 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብሩ የተገኙት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ ደሳለኝ ጣሰው÷ አሁን ላይ ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቋቋምና ሕዝቦቿን ለመታደግ  መተባበር ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!