የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ የሚያስመሰግን ነው-የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር

By Meseret Demissu

July 22, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አናያናሲ ሮድሪጎዝ ካሜጆ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም 46 ዓመት የዘለቀው የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ እና ዘርፈ-ብዙ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጤና፣ በአለም አቀፍ መድረኮች፣ በትምህርት እና በተለያዩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ሽብሩ ማሞ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማወጁንና የተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወቅቱ የእርሻ ጊዜ በመሆኑ ህዝቡ ተረጋግቶ ስራውን እንዲያከናውን ለማድረግ የታለመ ነው ብለዋል።

ነገር ግን አሸባሪው የህወሓት ኃይል ህፃናትን ጭምር ለውትድርና እያሰለፈ ውጊያ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኘ ለሚነሱ ወቀሳዎች የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖር አለመኖሩን የጋራ  ምርመራ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችም ገለጻ አድርገዋል።

በተጨማሪም  አምባሳደር ሽብሩ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉበት ነጻና ሰላማዊ ምርጫ ሆኖ መጠናቀቁን እና ኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗ፣ የግድቡ ግንባታ ለልማት እንጂ ማንንም የመጉዳት አላማ እንደሌለው፣ በታችኛዉ ተፋሰስ አገራት የፈጠረው ተፅእኖ አለመኖሩ እና ኢትዮጵያ፤ ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለው መሆኑንና በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የሚካሄደው ድርድር መፍትሔ ያመጣል ብላ እንደምታምን በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ መቆየቷን ለክብርት ምክትል ሚኒስትሯ ገለፃ አድርገዋል።

አምባሳደር አክለውም ኩባ በአለም አቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍ እና አጋርነት ለኩባ ሕዝብና መንግስት ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ምክትል ሚኒስትሯ በበኩላቸው÷ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር አሁንም በአለም አቀፍ መድረኮች እና በሌሎች በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልፀው÷ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሉ አለመግባባቶች በትብብር መንፈስ በሶስቱም አገራት ለውይይት ቅድሚያ ሰጥተው በመነጋገር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!