አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በምዕራብ አርሲ ዞንና ሻሸመኔ ከተማ በሰላም ግንባታና ግጭት ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎችን ተቋማዊ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በምዕራብ አርሲ ዞንና ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ከሚመለከታቸው የሰላም ባለድርሻ አካላት መካከል የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በስነ ስርአቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎቾና የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ የሰላም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በአካባቢው የሰላም ግንባታ ጥረት አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑን የጠቅላላ ጉባኤው ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ ገልፀዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ ምዕራብ አርሲ በተለይ ሻሸመኔ ላይ ደርሶ የነበረው የሰላም እጦት ጠባሳ ታሪክን ጥሎ ያለፈ እኛንም ያሳዘነና ያሳፈረ ነበር ብለዋል።
ሆኖም የሀይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች ባሉባት ሀገር ይህ መፈጠሩ ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያደርግ እና ሀላፊነትም መውሰድ አለብን ነው ያሉት።
ትውልድ ቀረጻ ላይ በአግባቡ ባለመሰራቱ ችግሮች እየተፈጠሩ በመሆኑ በትኩረት በመስራት ፣ አስተዳደጋቸዉንም በማስተካከል ለወደፊት መልካሙን ማበጃጀት ይኖርብናልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የምዕራብ አርሲ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤና የዞኑ ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የመግባቢያ ሰነዱ ባለቤቶች መሆናቸውን የጉባኤው የህግ አገልግሎት መምሪያ አቶ ማሞ ወጀጋ ገልፀዋል።
ለግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለግ ከአካባቢ የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ስልጠና መስጠትና የሰላም ኮሚቴ በየወረዳውና በቀበሌ ማዘጋጀት እንዲሁም መከታተል የመግባቢያ ሰነዱ ከያዛቸው ነጥቦች ተጠቃሾች ናቸው።
በመቅደስ አስፋዉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!