የሀገር ውስጥ ዜና

ለመከላከያ ሰራዊት ከወላይታ ዞን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

By Tibebu Kebede

July 23, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ዞን አስተዳደር ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያዘጋጀውን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር እና 20 ኩንታል በሶ እንዲሁም 400 ደርዘን ውሃ ድጋፍ ለክልሉ ሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ አስረከበ።

የወላይታ ህዝብ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የህውሃት /ጁንታ/ አሸባሪ ቡድን በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በማድነቅ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያዘጋጀውን ድጋፍ የደቡብ ክልል ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው፣ የደቡብ ብልፅግና ፖርቲ ሴቶች ሊግ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ነኢማ ሙኒርና የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በተገኙበት ነው ያስረከበው።

የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው የወላይታ ህዝብ ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው የክልሉ ህዝብ ለሰራዊቱ ደም ከመለገስ አንስቶ በአይነትና በገንዘብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ጁንታው ግጭቱ በሁለት ክልሎች ብቻ ነው እያለ የሚነዛውን ከፋፋይ አጀንዳ በማስቀረት ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በማስተዋል አሰፋ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!