አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም የአፋር ክልል ነዋሪ ህዝብ አሸባሪው ወያኔ ያወጀብንን ጦርነት ለመቀልበስ አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ከሰመራ፣ ሎጊያና ዱብቲ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት፤ የወያኔ ጁንታ ሀገሪቱን እኛ ካልገዛን እናፈርሳታለን በሚል እብሪት ተወጥሮ የአፋር ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ግንባር የጥፋት ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል።
የአፋር ክልላዊ መንግስትና ህዝብ በመከላከያ ሠራዊትና በሀገር ላይ የተቃጣ የእብሪት ጥቃት በራሱ ላይ የተፈጸመ መሆኑን በመገንዘብ በተጀመረው የህግ ማሰከበር እርምጃ ተገቢውን ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እርምጃ የተደናገጠውና ተስፋ የቆረጠው የህወሃት ጁንታ በቅርቡ አፋር አርብቶ አደሮች ላይ በከፈተው ጦርነት በንጹሃን ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን እንዲሁም ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል።
ይህም ለአፋር ህዝብ ያለውን ንቀት በግልጽ የሚያሳይ ክብረ- ነክ ተግባር በመሆኑ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊታችንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በጥምረት የጁንታውን ግብአተ-መሬት ያፋጥነዋል ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች ነጻነት በነጻ የማይገኝ መሆኑን አውቀው በተጀመረው ሀገር የማዳን ዘመቻ የአካባቢያቸውን፣ ክልላቸው ብሎም ሀገራቸውን ሉአላዊነት የማስከበር የተጣለባቸውን ታሪካዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።
ርዕሰ መስተዳደሩ ወጣቶች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማንቃትና በአንድነት ለአንድ ዓላማ በመሰለፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በራሳችን ተቀራርበንና ተናበን መስራት ይኖርብናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ወያኔ በእብሪት ተሞልቶ ምንም በማያውቁ ንጹህ የአፋር አርብቶ አደሮች ላይ በከፈተው ጦርነት ህጻናትና ሴቶች አዛውንቶች ሳይቀሩ ማጥቃቱን ተናግረዋል።
የጥፋት ቡድኑን ለማስወገድ መንግስት የሚሰጠውን ስምሪት በመቀበል ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመከፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ አሁን እየፈጸመ ያለው ግፍ ባለፉት 27 ዓመታት አፋርን ጨምሮ በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘርፎ ባጠራቀመው ሃብት መሆኑ የጭካኔውን ጥግ የሚያሳይ ተጨባጭ ሃቅ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!