የሀገር ውስጥ ዜና

በጎፋ ዞን ከ3ነጥብ 6ሚሊየን በላይ ብር እና የስንቅ ድጋፍ ተደረገ

By Meseret Awoke

July 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ሃምሌ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በደቡብ ክልል የጎፋ ዞን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ብር እና የስንቅ ድጋፍ ተደርጓል።

የጎፋ ዞን የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታመነ ቢሻው እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ አሸባሪው የህወሀት ቡድን ሀገርን ለማፈራረስ እያካሔደ ያለውን የሽብር ሴራ ለማክሸፍ እየተንቀሳቀሰ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማጠናከሪያ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ ታመነ፥ የዞኑ ህብረተሰብም ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀን መሆኑን ተናግረዋል።

ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከባለሀብቶች፣ ከከተማ ነዋሪዎች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከተቋማት፣ ከአርሶ አደሩ እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መሰባሰቡን ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ብልጽግና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተቃጣውን የሽብር ተግባር ለመከላከል የዞኑ ህብረተሰብ ወደ ግንባር በመሄድ አለኝታነቱን ለማሳየት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የጎፋ ዞን ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ጸጋነሽ እንግዳ ፥ አሸባሪው ጁንታ ህጻናትን በጦርነት እየማገደ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ እና የክልሉ ሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!