የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ከልል በአንድ ጀምበር  80ሚሊየን ችግኝ ይተከላል

By Feven Bishaw

July 27, 2021

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ከልል ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል በአንድ ጀምበር 80ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት  በሃላባ ዞን  ተከናውኗል፡፡

በክልሉ ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥም 300 ሺው  በሀላባ ዞን በአንድ ጀምበር ለመትከል መታቀዱ ታውቋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የተለያዩ  የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በክልሉ በርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ አምና በአንድ ጀምበር በክልሉ 77 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ መተከሉን አስታውሰው  ዘንድሮም በይበልጥ  እንደሚተከል ገልፀዋል፡፡

በዘንድሮ አመት ክልሉ 1 ነጥብ 57 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዶ ስራ የጀመረ ሲሆን እስካሁን 863 ሚሊየን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

የአግሮ ኢንደስትሪ ፣ የደን፣ የፍራፍሬ፣ የቀርከሃ፣ የመኖ ዕፅዋትና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

በፈትያ አብደላና በመቅደስ አስፋው