አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሕወሓት አጎራባች ክልሎች ላይ ተከታታይነት ያለው ትንኮሳ እየፈጸመ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
ቢለኔ ስዩም በዛሬው እለት ለሃገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም አሸባሪው ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በተከታታይነት ትንኮሳ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቡድኑ የግለሰቦችን ንብረት ማውደሙን እና መዝረፉንም ገልጸዋል፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም መድረሱን በመጥቀስም፥ ህወሓት ይህን የተኩስ አቁም በይፋ መጣሱንም አውስተዋል፡፡
ይህም በተለይም ለችግር የተጋለጡ እና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግና ከአካባቢው ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
በተያያዘም ስድስት ኤርትራውያን ስደተኞች በአሸባሪው ሕወሓት መገደላቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ባለፈም ቡድኑ ህጻናትን ለውትድርና በመመልመል ንጹሃንን እንደ መሸሸጊያ እየተጠቀመባቸው መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
መላው ህዝብም ይህንህ የአሸባሪውን ድርጊት በይፋ መቃወሙንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ መንግስት የደረሰውን የተኩስ አቁም አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!