የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

By Meseret Awoke

July 29, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረማርያም ከሰም ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

አደጋው የደረሰው ዛሬ ከጠዋቱ 2 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፥ በወረዳው ሸረር ከተባለ ቀበሌ 10 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ሃሙስ ገበያ በመጓዝ ላይ የነበረ ኮድ 3 ኦሮ 31605 የሕዝብ ማመላለሻ መኪና በግምት 180 ሜትር ገደል ዉስጥ በመግባቱ ነው ሲሉ የከሰም ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር የኋላሸት ተፈራ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በአደጋው የአራት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ፥ ሌሎች ሁለት ተሳፋሪዎች ወደ ሸኖ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እየተወሰዱ ባለበት ሰዓት ህይወታቸው አልፏል ብለዋል።

ተጎጂዎች በሸኖ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፥ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

በሰላም አሰፋ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!